ሦስተኛው አብዮትJune 12, 2025



Description
መግለጫ፡ ሦስተኛው የ40 ዓመት አብዮት የምንለምነውን አናውቅም ፡ የኢትዮጵያ የቆሰለ ተስፋ የግል ዶሴ! እኛ ኢትዮጵያን የምንመኘውን፤ የምንፈልገውንና ወደ እግዚአባሔር የምንለምነውን አናውቅም። እኔ ተወልጄ ያደግኩት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክፍል እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ ሕይወትን በመጋፈጥ ነበር። ብዙ የልጅነት ችግሮችን በመጋፈጥ በእግዚአብሔር እርዳታ በ1990 ዓ.ም. ዩንቨርሲቲ የመግባት እድል አግኝቼ አስደሳች የሥራ ዘመን አሳልፌአለሁ። እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን የተማርኩት በአዲስ አበባ ዪኒቭርሲቲ በሶሽዮሎጂ የትምህርት ክፍል ነው። ስለዚህ ስድስት ኪሎ ለእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ቅርብ ስለሆነ ፤ አንዳንዴ ከጓደኞቼ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ለብቻዬ የእንጦጦ ተራራን በእግሬ እየወጣሁ አልፎ አልፎ ቤተክርስቲያን እሳለም ነበር። በነገራችን ላይ የእንጦጦ ተራራን ለመውጣት ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ይፈጃል። ነገር ግን ጉዞው ሁሉጊዜ በጣም አስደሳች ነበር። እንጦጦ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ተራራማ አካባቢ ሲሆን ተራራውን በወጣሁ ቁጥር ሰማዩን በእጄ የመንካት ያክል ይሰማኝ ነበር። የደጋው ስሜት ቀዝቃዛ ቦታን ለሚወድ ለእንደ እኔ ዓይነቱ ሰው ደግሞ እጅግ መንፈስን ያረካል። ሚያዚያ ላይ ብትሔድ አየሩ ወተት የሚመስል ቀዝቃዛ ነው። እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ሂዶ ፀሎት ማድረግ እጅግ የሚያስደስት የመንፈስ ስሜት ይፈጥርልኝ ነበር። ሥራ ከጀመረኩም በኋላ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ እንጦጦ ማርያም እየሄድኩ ፀሎት አደርግ ነበር። ብዙ ችግሮቼም ተፈተውልኛል ፤ ከብዙ ፈተናዎችም ተርፌአለሁ፤ እግዚአብሔርም በመንገዴ ሁሉ እንዳለ አምናለሁ። ብዙውን ጊዜ መሄድ የምውደው ከቅዳሴ በኋላ ሁሉም ነገር ጸጥ ባለበት ሠዓት ነበር። አንዳንድ ጊዜ በራሴ ሕይወት ፤ በሥራ ቦታ ፤ በቤተሰብ የጨነቀ ጉዳይ ሲገጥመኝ ከጭንቀት ለመገላገልና እግዚአብሔር እንዲፈታልን ስፈልግ እንጦጦ ማርያም ሂጄ እፀልይ ነበር። አስታውሳለሁ የተወሰኑ ጊዜያት ፀሎቴ በእንባ ይታጀብ ነበር። በጣም ከማልረሳው የእንባ ፀሎቶች አንዱ በ2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ አገራችን በከፍተኛ የመውደቅ አደጋ በነበረችበት ወቅት ያደረግኩት ፀሎት ነበር። በወቅቱ ኦሮሚያ ክልል አምቦ አካባቢ ፕሮጀክቶች ስለነበሩን ሁኔታዎቹ እንዴት አስፈሪ እንደነበሩ አስታውሰለሁ። ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተስተጓጉለው ነበር። የቄሮ እንቅስቃሴ መፈናፈኛ አይሰጥም ነበር። ጃዋር አሜሪካ ሆኖ ማታ ላይ ይተነፍሳል፤ ጠዋት እዚህ ነገሮች ይበተናሉ። ማንም አስተማሪ ትምህርት ቤት መሄድ አይችልም ነበር። እናም አገሪቱ በተፈጠረው የፖሊተካ አለመረጋጋትና የወጣቶች በመንግሥት ላይ የነበራቸው ጥላቻ በግልጽ ይታይ ነበር። ደግሞ ለመሞት የነበራቸው ቁርጠኛነት በጣም አስገራሚ ነበር። ወጣቶች ገና ጠዋት ከቤት ሲወጡ ዛሬ ከሞትኩ ደህና ሰንብቱ ብለው ቤተሰባቸውንና ጓደኞቻቸውን ተሰናብተው ይወጡ ነበር ይባላል። መንሥትም የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝም የመፍትሔው አካል ለመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን ለቀቁ። ትክክል ነበሩ፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል። አንድ ኃላፊነት የሚሰማው መሪ ለዜጎች ደህንነት ሲል የፈጸሙት ጀግንነት የተሞላበት ድርጊት እንደ ነበር ይሰማኛል። እንደዚህ አድርጎ አገርን ከመምራት ሁሉም ነገር ቢቀር ይሻላል። ሁሉም አለቃ፤ ሁሉም ተሰሚ መሆን በሚፈልግበት ዓለም ሥልጣን አለኝ ከማለት ድሃ ሆኖ በመንገድ እንደ እብድ መለመን መንከራተት ይሻላል። ውሳኔያቸውም ትክክለ ነበር. በወቅቱ ብዙ ነገሮች ይጨንቁ ስለነበር ፤ በተለይ ሕጻናት እና ልጃ ገረዶች በአስቸጋሪ ውስጥ ስለነበሩ ፤ እኔም ለአገሬ መልካም ነገር ከመመኘት አንጻር በተለይ ስለአገሬ መጻይ ዕድል ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በወቅቱ በነበረው እጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለአገሬ መፍትሔ እንዲያመጣ ነገሮች ወደ መልካም እንዲሄዱ እንደ ማንኛውም ዜጋ ልመናየን ለእንጦጦ መርያም በልዑል እግዚአበሔር ፊት እያለቀስኩ ፀለይኩ። እሁድ ጠዋት እንጦጦ ሂጄ ማክሰኞ ዶ/ር አብይ አሕመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተሾሙ። ይኽ ደግሞ በትክክል በፀሎት ለእግዚአብሔር የለመንኩትና እንዲሆን የፈለግኩት፤ ሰውዬው ቢመረጥ ኢትዮጵያን ያሻግራታል ብዬ እርግጠኛ የሆንኩበት ፀሎት ነበር። እሰይ ፈጣሪ ይመስገን አልኩ። ፊቴም በደስታ በራልኝ። እንደዚህ ደስተኛ የሆንኩበት ምክንያት እስከአሁን ከልቤ ፀልዬ አምላኬን የጠየቅኳቸው ችግሮች ሁሉ በእመቤቴ ማርያም ምልጃ ፈጣሪ ሰምቶልኝ በመልካም ነገር ተፈጽመውልኝ ስለነበር ነው። በውጤቱም ጥርጣሬ አልነበረኝም። ነገር ግን አሁን ላይ ሆኘ ሳስብ ፤ ለካስ እኛ ኢትዮጵያውያን የምንጠይቀውን የምንለምነውን አናውቅም የሚል ነው። እንዴት? ይኽ በወቅቱ በነበረው ስሜት ስንመለከት እግዚአብሔር ፀሎቴን ሰማልኝ ማለት ነው። ደግሞም ለማ መገርሳና እና አብይ አሕመድ በወቅቱ በሁሉም ብሔሮች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነበሩ። ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው ላይ ላዩን ስንመለከተው ነገሮች እጅግ መልካም ይመስሉ ነበር። ይሄንን የሚክድ ሰው ያለ አይመስለኝም። እናም አገር በደስታ በሆታ በጭፈራ በድጋፍ ሰልፍ ተጨናነቀች። የሁሉም ክልሎች መስቀል አደባባዮች ለአብይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ ተጨናነቁ፡- ከጅጋ እስከ ጅጅጋ፤ ከሞያሌ እስከ መቀሌ ከጎንደር እስከ ባሕርዳር፤ ከአሶሳ እስከ አዋሳ፤ ከጅማ እስከ ዲማ፤ ከራስ ዳሽን እስከ ዳሎል በሁሉም ቦታ የሠላማዊ ሰልፍ ትርኢት እኔ እሻል እኔ አሻል መወዳደር ተጀመረ። አንድ ኪሎ ሜትር ሰንደቅ ዓላማ በብዙ ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቶ በአብይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ ተዘጋጅቶ ጊነስ ቡክ ላይ ሪከርድ የሰበረ ይመስለኛል። አገር በሙሉ ሰከረ። ሚሊኒየም አዳራሽ በሙዚቃ ድግስ ቀለጠ። ዘፈን በዘፈን ሆንን። ጠዋት ሲነጋ ይሄ ሙሴ የሆነ ሰውዬ በሠላም አድሮ ይሆን እንዴ? እያልን ነጋ ጠባ በሶሻል ሚዲያ መጠመድ ሆነ ውሎና አዳራችን። ሁሉም ሰው አበደ። አንዳንድ ቤት የወላጆች ፍቅር ተላብሶባቸው ሕጻናት ሁሉ አብይ አሕመድን በቴሌቪዥን መስኮት ሲያዩ በደስታ ይቦርቁ ነበር።አቤት የደስታ ጊዜ፤ አሁን እኮ ይሄ ትዝታ ሩቅ ይመስላል። በቦምብ ሁሉ ልንሞትለት እንፈልግ ነበር እኮ። በሰኔ 15ቱ የአዲስ አበበባው የቦምብ ፍንዳታ ድራማ ላይ እኔ ብኖርና ብሞትም ምንም አይመስለኝም ነበር። እውነት እኮ ነው ፤ ነገሮች እኮ ትክክል ይመስላሉ። ሰይጣን መልአክ መስሎ ይመጣል የተባለበት ዘመን ይኼ ይመስለኛል? የፍጻሜው ዘመን መጨረሻ የለውም። ወደ ቀደመ ነገራችን ልመለስና፡- እኛ ኢትዮጵያወያን የምንለምነውን አናውቅም የሚል ነው። ይኼ ነገሬ ትዝ ያለኝ እና በዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት የእኔ ለአብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ መለምንና አሁን እየሆነ ያለውን ነገር በመመልከት ነው። የመጨረሻ ዘመን የእብደት፤ ከኀሊና መሰወር መሆኑን የገባኝ በዚህ የአብይ ዘመን ነው። ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እምላለሁ! አብይ አሕመድ በኢሕዴግ ጉባኤ ማክሰኞ ሊመረጥ እሁድ ጠዋት እንጦጦ ማርያም ሂጄ፤ እሱ እንዲመረጥና ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆን በእግዚአብሔር ፊት ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ፀሎት አድርሻለሁ። ይኽ ኑዛዜዬ ምናልባት እኔ በሕይወት ባልፍ እንኳ የዚህ መጽሐፍ የታሪኩ መነሻና ታላቅ የአገር ዶሴ ሆኖ እንዲመዘገብልኝ እፈልጋለሁ።›› ዛሬ አብይ አሕመድ በአማራ ክልል፤ እኔ በምኖርበት አካባቢ ዘንባባ አንጥፎ በተቀበለው ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት አደጋ ያደርሳል ብዬ ግን አስቤው አልሜውም አላውቅም። የእኔ ፀሎት እኔንና አገሬን አደጋ ውስጥ ይጥላል ብዬ ለሰከንድም አስቤው አላውቅም። ስለዚህ አብይ በሚያደርሰው መከራ ውስጥ ሆኜ የወገኖቼን ጩኸትና የእናቶችን ለቅሶ እየሰማሁና እያየሁ ይሄንን ‹ሦስተኛ አብዮት› የሚለውን መጽሐፍ ለመጻፍ ተገደድኩ። ይኽ ፖለቲካ አይደለም። ይኽ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሆኜ ለአገሬ በልጅነቴ ጀምሮ ስመኝላት የነበረውን የእድገት መንገድ ለታሪክ ለተውልድ አስቀምጨ ለማለፍ ያደረግኩት አስተዋጽኦ ነው። አሁን ላይ ሆኘ የተገነዘብኳት አንዲት የመንፈስ መገለጥ ብትኖር የኢትዮጵያ ትንሳኤ በሆይታ፤ በፌሽታ ፤ በዘፈን ፤ በብዙ በድጋፍ ሰልፍ ወይም በሽለላና በቀረርቶ እንዳልሆነ ነው። አሁን የተገነዘብኩት የኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚመጣው በብዙ ፀሎት በረጅም ዘመን ሱባኤ መሆኑን ነው። ይኽ ሦስተኛው አብዮት ታሪክ የሚጀምረው "የምንለምነውን አናውቅም" በሚል የመንፈስ ቁጭት በመነሳት ነው። አሁንም በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም። አንተ የፈቀድከውን አድርግ፤ አንተ የፈቀድከውን ለንግሥና ቀባ ብሎ መፀለይ አሁን ለኢትዮጵያውያን አንገብጋቢ ፀሎት ነው። ከመራው አውጣን ብሎ መፀለይ አሁን የምቾት ሳይሆን የመንፈስ መንቃት ነው፤ ኢትዮጵያን ከመጥፋት አደጋ እንደ መታደግ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ፀልዩ! እነሆ ሦስተኛው አብዮት ከነማኔፌስቶ ጋር ለኢትዮጵያ ትንሰኤ!